በፌድራል ህገ መንግስቱ ስለአናሳዎች መብትና ጥበቃ

11/04/2021

በፌድራል ህገ መንግስቱ ስለአናሳዎች መብትና ጥበቃ
minorities right!

በፌድራል ህገ መንግስቱ ስለአናሳዎችና የአናሳዎች መብቶች በሚመለከት በግልፅ ዘርዘር ያለ ነገር ባይገልፅም በህገ መንግስቱ አንቀፅ 54(3) ስለተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሚደንግገው ስር የምክር ቤቱ አባላት ቁጥር በህዝብ ብዛትና በልዩ ትክረት ውክልና የሚሰጣቸው አናሳ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀጥር መሰረት በማድረግ ከ555 የማይበልጥ ሆኖ ከዚህ ውስጥ አናሳ ብሔረሰቦች ከ20 የማያንስ መቀመጫዎች እንደሚኖራቸው ይገልፃል። ዝርዝሩም በህግ ይደነግጋል ይላል። በፌድራል ህገ መንግስቱ በሌላ በኩል የአናሳ ብሔር መመዛኛና የቁጥር ልኬት ባያስቀምጥም ስለ የብሔር ብሔረሰብና ህዝብ መብት የሚገልፀው አንቀፅ 39(5) ሲያብራራ ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉ የጋራ ቋንቋ ያለቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የስነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልካምድር የሚኖሩ ናቸው ይላል። በዚህ ድንጋጌ ትርጉም ለብሔርም ለብሔረሰብም ለህዝብም በተመሳሳይ መልኩ ይገልፃል። በአንድ ሀገር ብሔር ብሔረሰብ ህዝብ ተብለው የተገለፁ ማህበረሰቦች በቁጥር ብዛት ተመሳሳይ የሚሆኑበት አገጣሚ ላይኖር ይችላል። ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ ህዝብ በማንንቱ ከሌላው ማንነት ጋር የተለየ እስከሆነ ድርስ የቁጥር ብዜት ሳይታይ የእኩልነት መብቱ ይኖራዋል። ቋንቋው ባህሉ ወጉን እና የማንንነት መገለጫው ሊያሳድግ፣ ሊያስፋፋ እና እንዲከበርለት የግድ ያስፈልጋል። በቁጥር ብዛት ያለው ብሔር ብሔረሰብ ህዝብ ከሌላው አናሳ ከሆነው ማህበረሰብ ጋር የማንነቱ መብት እኩል ሊከበር ይገባል። ለአብዛኛው የተሰጠ የማንነት መብት ለአናሳው መከልከል ሰብአዊም ዴሞክራሲያዊ መብት መከልከል ኢፍትሃዊነት ነው።

ይህ ድንጋጌ ለብዙሃንም ለአናሳው እኩል መብት የሚያጎናፅፍ ነው። ስለዚህም ብሔር ብሔረሰብ ህዝብ እስከሆነ ድረሳ የቁጥር ብዛት መላኪያ ሳይሆን የአናሳው የማንነት መብት የተከበረ ነው። የህገ መንግስቱ በመሰረታዊነት የቆመለት አላማም ነው። ሰለዚህም ብሔር ብሔረሰብ ህዝብ የራሳቸው በራሳቸው ማስተዳደር ህገ መንግስታዊ መብት እና የአለም አቀፍ ህግም ድጋፍ ያለው ነው።

የኢትዬጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም የግለሰብና የቡድን መብቶች እኩል ህገ-መንግስታዊ እውቅና እንዲያገኙ ያደረገ ነው፡፡ የኢትዬጵያ ህገ መንግስት በአንድ በኩልም ብሔር፣ ብሔርሰቦችና ህዝቦች ሉአላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸው እና ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲሁም የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን እስከ መገንጠለል ያለገደብ መብት የሚያስከብር በቋንቋቸው የመናገር የመጻፍ፣ ቋንቋቸውን የማሳደግና ባህላቸውን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪካቸውን የመንከባከብ መብት የሚያስተናግድ ሲሆን በሌላ በኩል የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች የተከበሩባት ሀገር መሆኗ በፌድራል ህገ-መንግስት አረጋግጧል፡፡ በዚህ መልኩ የኢትዬጵያ ፌድራሊዝም የቡድንና የግለሰብ መብቶች በተሟላ መልኩ የሚያስከብር ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ነው፡፡ የሃይማኖት ነፃነትም መብት ለሁሉም ሃይማኖቶች በእኩል የሚሰጥ እንጂ ብዙ የሃይማኖት ተከታይ ያላቸውን የሚመለከት አነስተኛ ተከታይ ያላቸውን የሚነፍግ ከሆነ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይፈጠራል፡፡ በመሆኑም የአናሳዎች መብት ጉዳይ የፍትሐዊነት፣ የእኩልነትና የዴሞክራሲያዊነት ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህም ነው የሀገራችን ህገ መንግስት የብሔር መብትን ለሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያረጋገጠው። በተለይም በአንቀጽ 39 የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዘብ በቋንቋው የመናገር፣ የመጻፍ ቋንቋውን የማሳደግ እና ባህሉን የመግለጽ ፣ የማዳበር የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት እንዳለው ይገልጻል፡፡ እነዚህ መብቶች የብሔረሰቡ ቁጥር ከግምት ሳይገባ ለሁሉም ብሔርና ብሔረሰብ የተረጋገጡ መብቶች ናቸው፡፡ በዚሁ አንቀፅ ማንኛውም የኢትዬጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት እንዳለው እና ይህ መብቱም በሰፈረበት መልክዓምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግስታዊ ተቋማት የማቋቋም እንዲሁም በክልልና በፌደራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን እንደሚያጠቃልል ተደንግጒል፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም የኢትዬጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብት ያለ ገደብ የተጠበቀ መሆኑን ይገልፃል፡፡ እነዚህ መብቶች ለብዙሃኑም ለአናሳውም ብሔርና ብሔረሰብ የተረጋገጡ መብቶች ናቸው፡፡ በተግባር እንደታየው እያንዳንዱ ብሔርና ብሔረሰብ በተለያዩ ደረጃዎች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ይገኛሉ፡፡ በፌደራል መንግስት ውሳኔ ሰጪ አካላትና ተቋማት ተመጣጣኝ እና ሚዛናዊ ውክልና ለአናሳ ብሔርና ብሔረሰብ ተረጋግጦ በቂ የፖለቲካ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በክልሎች ደረጃም የአናሳና ነባር ህዝቦች መብት በተለያዩ ደረጃዎች በተሟላ ሁኔታ በክልሎች ህገ መንግስት አውቅና አግኝተው ይከበራሉ። ለምሳሌ በአማራ ክልል የአገው ህምራ፣ የአገው አዊና ኦሮሞ ብሄሮች በአማራ የብሄረሰቦች አስተዳደር በሚል መዋቅር ራሳቸውን ያስተዳድራሉ። በብሄረሰቦች አስተዳደር ሦስቱ የመንግስት አካላትም በአግባቡ ተደራጅተዋል። በሦስቱም የብሄረሰብ አስተዳደር የየራሳቸው ቌንቌ የስራ ቌንቌ ነው። በክልል ህግ አውጪና አስፈጻሚ አካላት በቂ ውክልና አላቸው። በተመሳሳይ በደቡብም ብሄር ብሄረሰቦች በዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ።

ሦስቱ የመንግስት አካላትም በብሔረሰብ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በአግባቡ የተደራጁ ናቸው። በተለይም የብሄረሰብ ዞንና ልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች በደቡብ ምክር ቤት ባልተሸፈኑ ጉዳዮች ሕግ የማውጣት ሥልጣን አላቸው። በደቡብ ክልል ምክር ቤትና በደቡብ ክልል የብሔረሰብ ምክር ቤት አናሳ ብሄረሰቦች ዋስትና ያለው ውክልና አላቸው። በብሄረሰብ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የአናሳ ብሄሮች ቌንቌ የሥራ ቌንቌ ነው። ባህላቸውን ለማሳደግና ለማስፋፋት ህግ ማውጣት ይችላሉ። በጋምቤላ ክልልም እንዲሁ አኝዋክ፣ ኑዌርና መጀንግር(በክልሉ 4%የሆኑት) አናሳና ነባር ብሄሮች በጋምቤላ ህገ መንግስት በብሄረሰብ ዞኖች የራስ ገዝ ሥልጣን አላቸው። እንደ አማራና ደቡብ ሦስቱ የመንግስት አካላት በአግባቡ ተደራጅተዋል። ቌንቌቸው በየዞናቸው የሥራ ቌንቌ ነው። በቤነሻንጉል-ጉምዝ ክልልም እንዲሁ የአናሳና ነባር ብሄሮች የቌንቌ፣ ባሕልና ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ መንግስታዊ መብት የተከበረ ነው። በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መሰተዳደርም ለአረጎባ ብሔረስብ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተድሩበት መብት ተግባራዊ ሆኗል። የሀረሪ ህዝብ ክልልም የሀረሪ ብሔር ማንነት፣ ታሪክና ባህል መሰረት ባደረገና የክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ ባመዛዘነ መልኩ በአናሳነት ሊዋቀር ችሏል። በፌዴራል ህገ መንግስት ብዙሃንም አናሳም በማንነት እና የራስ በራስ የማስተዳደርና የመወሰን ጉዳይ እኩል መብት አላቸው።

በኢትዮጵያ ለአናሳዎች ክልላዊ፣ ዞናዊና ወረዳዊ ራስን በራስ የመስተዳደር መብት ያገናፀፈ ቢሆንም በብዝሃነት ውስጥ የአነሳዎች መብት በምን መልኩ ይጠበቃልና ይከበራል የሚለው ጉዳይ በህገ መንግስቱ በግልፅ የተቀመጠበት ሁኔታ አለመኖር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ያለ መኖር የራሱ አሉታዊ ችግር ፈጥሯል። ለአናሳዎች የሚሰጥ መብቶች እንደ አሉታዊና እንደ አድሎ በመቆጠር የጥላቻና የጥቃት ተጋላጭም አድርጎቸዋል። ሰለዚህም የአናሳዎች መብት በምን መልኩ ሊጠበቅ ይችላል የሚል አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከ97%-98% የሚሆኑ ሀገር አቀፍ አናሳዎች (national minority) እና ክልላዊ አናሳዎች (regoinal minority) በተዛማች(relatively) አናሳዎች ይገኛሉ። ከዚህ በፊት ለመግለፅ እንደተምከረው የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህግጋትና ስምምነቶች አብዛኛውን የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ተቀብሎት አፅድቆታል። ሰለዚህም ህገ መንግስቱ ሲቶረጎም የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህግጋትና ስምምነቶች ጋር በተጣጠመ መልኩ መተርጎም እንዳለበት ያስገድዳል።

by Mahir Ibrahim Shami

Back to News Page

About Us

Australian Saay Harari Association is a non profit, ethnically based, social organization based in Melbourne, Australia.

Our Contacts

61 Elm Park Dr, Hoppers Crossing
Victoria 3029, Australia

(+614) 018 06 589
(+614) 1364 1816